የ2023 አባልነት ክፍያዎን በባንክ ወይም በቪፕስ እንዲያስገቡልን በትህትና እንጠይቃለን።
ባንክ፤ 05401729420
ቪፕስ፤ 500424
የዓመታዊ ክፍያ መጠን፤
ለአዋቂ፤ ከ200 ክሮነር አንስቶ
ለህጻናት፤ 80 ክሮነር።
ክፍያውን ሲፈጽሙ "medlemskontingent" የሚለውን መልዕክት ያካቱበት።
ቅድመ ዝግጅትና ሁኔታዎች፤
ቅድመ ዝግጅትና ሁኔታዎች፤

በስደት የምንኖር ኢትዮጵያዊያን የፈለግነውንና የተመኘነውን የስራ አይነት በሙያችን ለማግኘት የተለያዩ እንቅፋቶች ያጋጥሙናል፡፡ በተለይ የመኖሪያ ፈቃድ የሌለን በምንሆን ጊዜ ደህና የሆነ ስራ በሙያችን ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ በዚህም ላይ ደግሞ ጸጉረ ልውጦች ስለሆን ቀጣሪዎች ጥርጣሬ ይገባቸዋል፡፡ ቀጣሪዎች እኛን ስራ ለመስጠት ቢፈልጉ እንኳን ያገሬው ሰራተኞች አይፈልጉ ይሆናል በማለት ከመቀጠር የሚቆጠቡበትም ጊዜ አለ፡፡
አብዛኛው ስራ የሚገኘውም በዝምድና፣ በትውውቅና በጓደኝነት ነው፡፡ ከዛ የተረፈ የስራ ኣይነት ማስታወቂያ ላይ ይወጣል። ትውውቅና ጓደኝነትም ለመፍጠር አጋጣሚው መፈጠር አለበት፡፡ ይኸን አጋጣሚ እራሳችን ከጊዜ ጋር ለመፍጠር ሊሳካም ላይሳካም ይችላል።
በተጨማሪም ስዴት ላይ ሆኖ ተስማሚና የሚወደድ ስራ ለማግኘት ሂደቱ ውስብስብ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ግን ስራ ለማግኘት ተጨማሪ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ታዲያ ይህንን ውስብስብ የሆነ ጉዞ እንዴት እንወጣዋለን? ስራ የማግኘት እድላችንን እንዴት ማስፋት እንችላለን? ያገሩን ባህልና ቋንቋ ከሞላ ጎደል መቻል፣ የህዝቡን ያኗኗርና የአቀራረብ ዘይቤን ማወቅ ደህና ስራ ለማግኘት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ይኸን ማወቅ ስራ ከማግኘት በተጨማሪ በግል ህይወታችንና በሌሎች የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በዕውቀት እንዲንዳብር ያግዘናል፡፡
በትውውቅ፣ በጓደኝነትና በዝምድና ተይዘው ያላለቁ ክፍት የስራ ቦታዎች ማስታዎቂያ ላይ ይወጣሉ፡፡ ማስታወቂያው ጋዜጣ፣ መጽሄት፣ ኢንተርኔት ወዘት ላይ ሊሆን ይችላል። በማስታወቂያው ላይ ስለመስሪያ ቤቱ፣ ስለ ስራው አይነት፣ ምን አይነት የስራ ልምድ ያለው ሰራተኛ እንደሚፈለግ ባጭሩ መጥቀስ የተለመደ ነው፡፡ አመልካቾችም ከደወሉ ደግሞ ማንን ማናገር እንደሚቻል ከስልክ ቁጥር ጋር ይገለጻል፡፡
ይኸን አጭር የስራ ማስታወቂያ በጥንቃቄ ረጋ ብሎ ማንበብና መረዳት በጣም ይጠቅማል፡፡ ማስታወቂያውን አንብበው ወዲያውኑ ማመልከቻ ከጻፉ ስራ የማግኘትዎ እድል በጣም የጠበበ ነው። ከዛ በፊት ግን በቅድሚያ ማድረግ ያለብዎትን ነገሮች በዝርዝር እናያለን፡፡ ምክንያቱም ማስታወቂያው ላይ በሰፈረው መረጃ ብቻ ማመልከቻ መላክ ስራውን ማግኘት ቀርቶ ለቃለ ምልልስ እንኳን ለመጠራት እድሉ ጠባብ ነው፡፡
አንድ የስራ ማስታወቂያ በወጣ ጊዜ በአስሮችና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰወች ያመለክታሉ፡፡ የአመልካቾች ቁጥር በጨመረ ቁጥር ውድድሩም ይብሳል፡፡ ታዲያ ማስታወቂያውን አንብበው በጥሞና ከተረዱ በኋላ ወደ መስሪያ ቤቱ ደውለው የሚመለከተውን ግለሰብ ማናገር ይጠቅማል፡፡ ከመደወልዎ በፊት ዝግጅ ማድረግ አለብዎት፡፡ ሲደውሉም ስልኩ በጸሃፊ ከተነሳ ማን እንደሆኑ፣ ለምን እንደሚደውሉና ከማን ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ ባጭሩ መግለጽ ተገቢ ነው፡፡ማስታወሻ!
አንዳንድ ስራ ቀጣሪዎች እጩ ሰራተኛ ለማግኘት ደላላ ወይም "አዕምሮ አዳኞች" የሚባሉ ጋር ግንኙነት አላቸው። የዚህ አይነት ሁኔታ ካለ እዛው ማስታወቂያው ላይ ያገኙታል። ስለዚህ እርስዎ በቀጥታ ወደ ቀጣሪውም ሆነ ደላላው ዘንድ ከደወሉ የት እንደሚደውሉና ከማን ጋር እንደሚነጋገሩ ቢለያይም የስልቱ አይነት ግን ይመሳሰላል፡፡
ማነጋገር ከሚፈልጉት ግለሰብ ጋርም በተገናኙ ጊዜ፤ “ እንደምን ዋሉ! ስሜ እከሌ ይባላል፡፡ የምደውለው ከዚህ ቦታ ነው፡፡ የመጣሁት ከዚህ አገር ነው (እንደ ሁኔታው ቢለያይም ይኸን ማሳወቅ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም።) ያወጡትን የስራ ማስታዎቂያ አይቸዋለሁ፡፡ ስራው ይህንንና ይህንን ስለሚመስል እኔም የዚህ አይነት ልምድ ወይም ፍላጎት ስላለኝ ይስማማኛል፡፡ ማመልከቻም ለመላክ አስቤአለሁ፤ ” ካሉ በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎችን ይጠይቁ፡፡ ይኸ የስልክ ንግግር በሚካሄድበት ጊዜ ረጋና ቀስ ብለው ባጭሩና በግልጽ ቋንቋ ቢናገሩ ሰሚው በቀላሉ ይረዳዎታል፡፡ በመካከል ሰሚው በሚናገር ጊዜ እንዳያቋርጡት ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ የዚህ ንግግር አላማ ማመልከቻ ከመላክዎ በፊት እርስዎን ባጭሩ ለማስተዋወቅ ነው እንጂ ብዙ ወሬና ኮተት አያብዙ፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ባጭሩ ጥሩ ትዝታ ጥለውና አመስግነው ንግግሩን ለመጨረስ ይሞክሩ፡፡ ያናገሩትን ሰው ስምና ቀኑን ያስታውሱ!
ፋንታው ተሰማ
ለ ኢትዮጵያውያን ማህበር በኖርዌይ፡፡
Add new comment