ልብስና አቀራረብ ከማየታችን በፊት አንዳንድ ሊጠየቁ የሚችሉ ጥያቄዎችን በዝርዝር አብረን እንይ፡፡ ብዙ አይነት ጭያቄዎች አሉ፡፡ እንደ ስራው አይነት እና ፀባይ ይለያያሉ፡፡ ከታች የቀረቡት ጥያቄዎች ሊጠየቁ የሚችሉ ጥያቄዎች ናቸው፤
1. ስለ መስሪያ ቤታችን ምን ያውቃሉ?
2. እርስዎን ለምን እንቀጥረዎታለን?
3. ምን አይነት አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ?
4. ከአምስት አመታት በኋላ እራስዎን እንዴት ያዩታል?
5. ጠንካራ ጎንዎ ምንድነው?
6. ደካማ ጎንዎ ምንድነው?
7. አሁን ምን እየሰሩ ነው?
8. ደመወዝ ስንት እንዲሆን ይፈልጋሉ?
1. ስለ መስሪያ ቤታችን ምን ያውቃሉ?
ስለ መስሪያ ቤቱ ለማወቅ ለቃለ መጠይቅ በተጠሩ ጊዜ አንዳንድ ቁልፍ መረጃዎች ፈልጎ ማግኘት ይቻላል፡፡ ከነዚህ መረጃዎች አንዳንዶቹ፤ መስሪያ ቤቱ ከተመሰረተ ስንት ጊዜ እንደሆነው፣ ምን አይነት አገልግሎት እንደሚሰጥ እና ምን አይነት ምርት እንደሚያቀርብ፣ ደንበኞቹ እነማን እንዴሆኑ፣ ስንት ሰራተኞች እንዳሉት ወዘተ ናቸው፡፡ የምንኖርበት ዘመን ውስጥ መረጃ በቀላሉ ስለሚገኝ፤ መስሪያ ቤቱን በመጠኑ ለማወቅ የተለያዩ ምንጮች መጠቀም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ መስሪያ ቤቱ የራሱ የኢንተርኔት ገጽ ሊኖረው ስለሚችል ብዙ መረጃ ይገኛል፡፡ ይኸ ካልሆነ ግን ሌላ የጽሁፍ መረጃ መፈለግ ይቻላል፡፡ ሰውም መጠየቅ ይቻላል፡፡
2. እርስዎን ለምን እንቀጥረዎታለን?
መስሪያ ቤቱ እርስዎን መርጦ ለምን ስራውን እንዲሰጥዎት ጉረኛ ሳይመስሉ ታታሪ ሰራተኛ መሆንዎን ማስረዳት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ ስራው ከርስዎ ትምህርት፣ ፍላጎትና ልምድ ጋር የተያያዘ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወደፊትም ለማደግና ለመሻሻል ስለሚፈልጉ ስራው ለርስዎ ጥሩ በር ከፋች መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ለስራው እርስዎ ተስማሚ እጩ መሆንዎን ማሳመን ይችላሉ፡፡
3. ምን አይነት አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ?
ከአዲስ አካባቢና ሁኔታ ጋር ባጭር ጊዜ ውስጥ እራስዎን የማለማመድ ልምድ እንዳለዎት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ተጨባጭ የሆነ ውጤት ለማስገኘት ታታሪ ሆነው እንድሚሰሩ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመስሪያ ቤቱ ላይ ለውጥ አመጣለሁ እንዳይሉ ግን ይጠንቀቁ፡፡ ገና ምን እንደ ሚጠብቅዎት አይታወቅም፡፡ በኋላ እንደ ሁኔታውና እንደ ስራው ድርሻ ይደረስበታል፡፡ በኋላም ቢሆን በተግባር እንጂ ለውጥ አመጣለሁ እያሉ አይደለም። በተለይ የመጀመሪያ ትውውቅ ላይ ለውጥ አመጣለሁ ማለት ጥሩ ቋንቋ አይደለም፡፡
4. ከአምስት አመታት በኋላ እራስዎን እንዴት ያዩታል?
ከአምስት አመታት በኋላ ምን እንደ ሚመስሉ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ ወገኛ ስራ ቀጣሪዎች ግን ሊፈታተኑ ይፈልጋሉ። ቢሆንም ግን የተለያየ አላማ ሊኖርዎት ይገባል፡፡ ለምሳሌ ስለቤተሰብ፣ ስለስራ፣ የተለያዩ ነገሮችን ስለማድረግ እና ስለ ስኬታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ህይዎት በራሷ ትምህርት ቤት ነች፡፡ ስለዚህ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ጊዜ ውስጥ በተለያየ ነገር ላይ የበለጠ በእውቀት እንደ ሚዳብሩ መግለጽ አይከፋም፡፡
5 እና 6. ጠንካራና ደካማ ጎን፤
ከደካማ ጎን ይልቅ ስለ ጠንካራ ጎን መናገር ይቀላል ይመስለኛል፡፡ ጠንካራ ጎንዎን ሲናገሩ ጉራ እንዳይመስል ጓዴኞቼ እንዲህና እንዲህ ይሉኛል ማለቱ ይሻላል፡፡ ለምሳሌ በማዳመጥ፣ በፍላጎት፣ የትርፍ ጊዜ አጠቃቀምና እንቅስቃሴ፣ አቀራረብዎ፣ የተለያዩ እይታዎች ወዘተ በተመለከተ ሊሆን ይችላል፡፡ ገንቢ አስተሳሰብና ግልጽ አቋም ካለዎት ደግሞ ይኸን መጥቀስ ይጠቅማል፡፡
ሰው የራሱን ደካማ ጎን ለመናገር ከሆነ ግን ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ግን ሰው ፍፁም አይደለምና ሁላችንም ደካማ ጎን አለን፡፡ ይኸን ሲናገሩ ግን ድፍን ያለ ደካማ ጎንዎን መናገር ተገቢ አይደለም፡፡ አባባሉና አቀራረቡ ላይ ብልሃት ያስፈልገዋል፡፡ ለምሳሌ ወደ ትልቅ ከተማ ስሄድ ፎቆች መቁጠር ስለምወድ እንቅፋት ይመታኛል፡፡ መንገደኞችም ጋርም መጋጨት ለምዶብኛል ማለት እልም ያለ ሁለት አይነት ሞኝነት ነው፡፡ በምትኩ ግን “ ጓደኞቼ ግትር አይነት ነህ፤ ምክንያቱም አንድ ጊዜ የተባለውና የታቀደው ነገር ሳያልቅ በቂ እረፍት አታደርግም " ይሉኛል ማለቱ ይሻላል፡፡ ግትር አይነት ቢሆኑም በዕቅድ እንደሚመሩ ያሳያል፡፡ የስራ ቀጣሪው በጥያቄው መልስ ላይ ምቾት እንዲሰማው ለማድረግ ነው፡፡ ምሳሌው ግልጽ እንደሆነ ተስፋ አለኝ፡፡
7. አሁን ምን እየሰሩ ነው?
ስራ ቀጣሪወች ሊቀጥሩት ያሰቡት ግለሰብ አሁን ምን እንደ ሚያደርግ በግልጽ ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ይኸን ከተጠየቁ አሁን የሚያደርጉትን እና የሚሰሩትን በግልጽ ማስረዳት ይጠበቅበዎታል፡፡ ስራ የሚቀይሩም ከሆን አሁን ያሉበት የስራ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ ከጎኑ ደግሞ ስፖርት የሚሰሩ ከሆነ ስፖርት እሰራለሁ ማለቱ አይከፋም፡፡ አካልዎ ሲታይ ግን ስፖርት የማይሰራ ሆኖ ማጋለጥ የለበትም፡፡ ገና ከት/ቤት የወጡ ከሆነ ደግሞ ስለመጨረሻው ትልቁ ፕሮጀክትዎ ዙሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ስራ ብቻ የሚፈልጉ ከሆነ፤ የከተማ አውደልዳይና የቤት አይጥ እንዳይመስሉ የተለያዩ ነገሮችን እንደ ሚያደርጉ መጥቀስ አይከፋም፡፡ ለምሳሌ በጎ አድራጎት ሊሆን ይችላል፡፡ የሚጽፉ ከሆነ መጻጻፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን አሁን ስራ ባይኖረዎትም ለራስዎ እና ለአካባቢዎ የሚጠቅም ነገር ማድረግዎን ለማሳየት ነው፡፡ ተሳታፊ መሆነዎን ለማሳወቅ ነው፡፡ አሁን ስራ ባኖርዎትም ጊዜውን በከንቱ እንደ ማያጠፉ የቀጣሪወቹ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡
8. ደመወዝ ስንት እንዲሆን ይፈልጋሉ?
ደመወዝስ? ጥያቄው አስቸጋሪ ነው፡፡ ለቃለ መጠይቅ ከመምጣትዎ በፊት፤ ስለ መስሪያ ቤቱ አጣርተው ከሆነ የደመወዙን መጠንና አካባቢ ያውቁታል፡፡ ከት/ቤት በቅርቡ የጨረሱ ከሆነ፣ የስራ ልምድ ካለዎት፣ የመስሪያ ቤቱ አይነትና ሃብት፣ የሰራው አይነትና ሃላፊነት የደመወዙን መጠን ይወስነዋል፡፡ ቁጥር ከመጥራት በፊት ግን “ለኔ ለእድገት በር ከፋችና የምወደውን ስራ ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይኸን ስራ ለማግኘት ያመለከትሁት ለዚሁ ነው “ ብለው ቢጀምሩ ነገሮች አይካበዱም፡፡ ቁጥር መጥራት ካስፈለገም ምክንያታዊ ሆኖ ጥሩ ደመወዝ መጠየቅ አይጎዳም፡፡ ምናልባት የስራ ማስታወቂያው ላይ የደመወዙ ልክ ቀርቦ ከሆነም ቀጣሪዎች ቃለ መጠይቅ ላይ ሊያነሱት ይችላሉ፡፡ አነስተኛ ደመወዝ መጥቀስ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም የስራ ለማኝ ያስመስላል፡፡
የቃለ መጠይቅ አቀራረብና ልብስ ቀጣዩ ገጽ ላይ፤
This policy contains information about your privacy. By posting, you are declaring that you understand this policy:
This policy is subject to change at any time and without notice.
These terms and conditions contain rules about posting comments. By submitting a comment, you are declaring that you agree with these rules:
Failure to comply with these rules may result in being banned from submitting further comments.
These terms and conditions are subject to change at any time and without notice.
የተሰጡ አስተያየቶች